ቅዱስ ቂርቆስ ወቅድስት እየሉጣ

Download PDF

ጥር 14 — ዕረፍቱ ለቅዱስ ቂርቆስ

ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት እየሉጣSt. Gabriel

ቅዱስ ቂርቆስ ዕድሜው የሦስት ዓመት ሳለ እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ ከሮሜ ወደ ሌላ ሃገር ሸሽታ ይዛው ሄደች በዚያም የሸሸችውን መኮንኑን አገኘችው። የሚያውቋትም ሰዎች ሸሽታ እንደመጣች ስለተረዱ ለመኮንኑ ነገር ሰሩባት። መኮንኑም ቅድስት አየሉጣን አስጠራትና ስለ አምልኮ ጠየቃት። ቅድስት ኢየሉጣም “መኮንን ሆይ፡ ዕድሜው ሦስት አመት የሆነው ሕፃን አለ አማልክቶችህን ማምለክ መልካም እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ያስረዳን ዘንድ እርሱን ጠይቅ” አለችው።

ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስም ወደ አለበት ጭፍራውን ልኮ ወደ እርሱ አስመጣው ሕፃኑንም ፊቱ ብሩህና ደስተኛ እንደሆነ አየውና “አንተ ደስተኛ ሕፃን ሆይ እንዴት ነህ?” አለው። ሕጻን ቅዱስ ቂርቆስም መለሰለት እንዲህም አለው። “አዎ እኔ በጣም ደስተኛ ነኝ ደስታዬም ተጠብቆልኛል። ላንተ ግን ሐዘንና ለቅሶ ጥርስ ማፋጨትም ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስም ለዝንጉዎች ተድላ ደስታ የላቸውም ብሏልና” አለው። እግዚአብሔር አምላክ ኃይልንና ንግግርን ሰጥቶታልና በዚያ ለተሰበሰቡት ሰዎች እስኪደነግጡ ድረስ ብዙ ተናገረ። ሕፃን ቅዱስ ቂርቆስም ንጉሱን መኳንንቱንና ጣዖታቱን ረገማቸው ከብርታቱም የተነሳ አደነቁ።

መኮንኑም በአፈረ ጊዜ በየዓይነቱ በሆነ ስቃይ፡ ታላላቆች እንኳ የማይችሉትን ታላቅ አስጨናቂ የሆነ ስቃይን አሰቃየው። እናቱ ቅድስት ኢየሉጣንም ከ እርሱ ጋር እንደ እርሱ በጣሙን አሰቃያት። እግዚአሔብሔር ግን ያለ ምንም ጉዳት ያነሳቸው ነበር። ብዙዎች አህዛብም ይህን አይተው አደነቁ ክብር ይግባውና በጌታችን በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት አምነው በሰማእትነት ሞቱ የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበሉ። በሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ላይም የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አደረበት። ታላላቅ ድንቅ ተአምራቶችንም ያደርግ ነበር። ብዙዎች በሽተኞችንም ያድናቸው ይፈውሳቸው ነበር። ይህንን ያየ መኮንን በታላቅ የናስ ጋን ውስጥ ውሃ ጨምረው በእሳት ያፈሉት ዘንድ አዘዘ። የፍላቱም ድምጽ እንደ ክረምት ነጎድጓድ ሆነ ድምጹም በጣም ያስተጋባ ነበር። ይህን ያየችና የሰማች እናት ቅድስት ኢየሉጣም ፍርሃትና የሃይማኖት ጉድለት ታየባት። ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ግን እናቱ ቅድስት ኢየሉጣን ሁኔታዋን አይቶ ወደ አምላኩ እግዚአብሔር ጸለየ። ያን ጊዜ ልዑል እግዚአብሔር ልቧን ወደ ሰማይ አሳርጎ ለቅዱሳን ሰማዕታት የተዘጋጁ የብርሃን ማደሪያዎችን አሳያት። ቅድስት ኢየሉጣም እንደገና በሃይማኖቷ ጸናች። እግዚአብሔር አምላኳንም አመሰገነችው። ልጇን ሕፃኑን ቅዱስ ቂርቆስንም “ልጄ ሆይ አንተ ከእንግዲህ አባቴ ነህ እኔም ልጅህ ነኝ” አለችው።

ቅድስት እየሉጣም ለልጇ “ያች የተወለድክባት ዕለት ቀኗ የተባረከችና የተቀደሰች ናት” አለችው። የመኳንንቱ ጭፍሮችም እሳት ወደ አለበት ጋኖች ውስጥ ቅዱስ ቂርቆስንና እናቱን ቅድስት ኢየሉጣን በጨመሯቸው ጊዜ የውሃው ፍላት ወደያውኑን ቀዘቀዘ። ከእግዚአብሔር የታዘዘ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወርዶ የእሳቱን ኃይል አቀዝቅዞታልና። ይህን ያየ መኮንን ሥጋቸው ተቆራርጦ እስከሚወድቅ ድረስ በመቃጥን ውስጥ አድርገው አንዲጎትቷቸው አዘዘ። ከእግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል አዳናቸው። መኮንኑም በታላቅ ስቃይ ያሰቃያቸው ዘንድ አስቦ እስኪመክር ድረስ በወህኒ ቤት ዘጋባቸው። በዚህን ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሕጻኑ ቅዱስ ቂርቆስን አረጋጋው አጽናናው ስሙን ጠርተው መታሰቢያ ለሚያደርጉለትም በረከትን እንደሚያገኝና ሌላ ብዙ ቃል ኪዳን ሰጠው።

ሲነጋ መኮንኑ ከመካነ ምኩናኑ ተቀምጦ ካለበት አስጠርቶ “የተመለስከው መመለስ አለን?” አለው:: ቅዱስ ቂርቆስም “አይሆንም አልመለስም” አለው:: ሰይፍ ጃግሬውን ጠርቶ “ንሳ ውደቅበት” አለው:: በሰይፍ መታው: ጌታም ነፍሱን ከመካነ ዕረፍት ሥጋውንም ነጥቆ በሰረገላ ኤልያስ አኑሮለታል:: እናቱ ቅድስት ኢየሉጣንም በማግስቱ (ጥር 16) በሰይፍ አስመትቷት በሰማዕትነት ዓርፋለች::

እግዚአብሔር አምላካችን የሕጻኑ ቅዱስ ቂርቆስና የእናቱ የቅድስት እየሉጣን በረከታቸውንና ረድኤታቸውን ያድለን አሜን።