ነገረ ቅዱሳን
- ‹‹ነገር›› ማለት፡- በቤተክርስቲያን የአንድነት ትምህርት ሙሉ መግለጫ በመሆን ያገለግላል፡፡
- በዚህ ነገር ስንል ስለአንድ ነገር የሚናገር፣ የሚያስረዳ፣ የሚተርክ ለዛ ለሚነገርለት ነገር እንደመግለጫ አስረጂ ሆኖ የሚቀርብ ቃል ነው፡፡
ቅዱስ ማለት
- ‹‹ቅዱስ›› ማለት ‹‹ቀደሰ›› ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ትርጉሙም ለየ፣ አከበረ፣ አመሰገነ፣ አገነነ፣ መረጠ፣ አጠራ፣ አነጻ፣ ባረከ ወዘተ … ማለት ነው፡፡
- በመሆኑም ቀደሰ ሲል ከርኩሰት፣ ከኃጢአት መንጻት፣ በማየ ቅድስና መንጻት (መታጠብ)፣ መአዛ ኃይማኖት ሆኖ መገኘትና፣ ለመልካም አገልግሎት በቅብዐ መንፈስ ቅዱስ ተቀብቶ ብቁ መሆን ማለት ነው፡፡
ቅድስና ራሱ በሁለት ይከፈላል
1. የባህሪ ቅድስና
- የባህሪይ ቅድስና ገንዘብነቱ ለእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ቅዱስ የሚለው ቃል ከሁሉ በፊት የሚያገለግለው ለእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡
- ይህ ስም የእግዚአብሔር የባህሪዩ መገለጫ ሆኖ የሚጠራበት ስያሜ ሲሆን ቅድስናው ከእርሱ የማይለይ ከማንም ያልተቀበለው፣ ያልተዋሰው ማንም ሊወስድበት የማይችል የራሱ ገንዘብ ማለት ነው፡፡
ዘሌ. 19÷2 ‹‹እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ›› እንዲል፡፡
መዝ. 137÷2 ‹‹ወደቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፤ ስለምህረትህና ስለ እውነትህ ስምህን አመሰግናለሁ፤ በሁሉ ላይ ቅዱስ ስምህን ከፍ ከፍ አድርገሀልና›› እንዲል፡፡
2. የጸጋ ቅድስና
- ‹‹ጸጋ›› ማለት፡- ቸርነት፣ በጎነት፣ ምህረት፣ ያለብድራት፣ ያለዋጋ የሚደረግ ስጦታ ማለት ነው፡ በመሆኑም የጸጋ ቅድስና ስንል ከእግዚብሔር በጸጋ (በስጦታ) የተሰጠ ወይም የተገኘ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛው ከእግዚአብሔር የሚገኝ ሃብት ሁሉ የጸጋ ቅድስና፣ የጸጋ ሀብት ይባላል፡፡
መዝ. 32÷5 ‹‹ጽድቅና ፍርድን ይወድዳል የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች››
ሮሜ 8÷28 ‹‹እግዚአብሔር ለሚወድዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን›› እንዲል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ኃይለ ቃላት ውስጥ ቸርነት፣ በጐነት እያለ የተጠቀሰው የእግዚአብሔር የባህሪይ ገንዘቡ ስለሆነውና ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች ስለሚሰጠው የጸጋ ቅድስና ነው፡፡ ስለዚህ የቅድስና ጥሪ ለሰው ዘር ሁሉ የተላለፈ ጥሪ ቢሆንም የተቀበሉትና በሕይወት የኖሩበት ጥቂቶች ናቸው፡፡
ማቴ. 22÷14 ‹‹የተጠሩ ብዙዎች፣ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና›› እንዲል፡፡
ነገረ ቅዱሳን ማለት ምን ማለት ነው?
‹‹ነገረ ቅዱሳን›› ማለት፡- ቅዱሳን ከልደታቸው እስከ እረፍታቸው ድረስ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ሕገ እግዚአብሔርን አክብረው፣ ትእዛዙን ፈጽመው የኖሩና የሚኖሩ የእግዚአብሔር ልጆችን እንዲሁ የቅዱሳንን መላእክትን ነገር የምንማርበት ትምህርት ቤት ነው፡፡
አንድም ነገረ ቅዱሳን ስንል፡- ኃይማኖት ይዘው ምግባር ሠርተው በስርዓት ተጉዘው እስከሞት ድርስ ታምነው ለተገኙ የእግዚአብሔር ወጃጆች፣ ንጹሐን መላእክት ክብሩን እንደገለጸላቸውና እንደሚገልጽላቸው የሚያስረዳን ነው፡፡
ነገረ ቅዱሳንን መማር (ማወቅ) ለምን አስፈለገ?
- ነገረ ቅዱሳንን ስንማር ከቅዱሳኑ ታሪክ ባሻገር የቅዱሳንን ሁሉ አስገኚ፣ የቅዱሳን ሁሉ ክብርና አክሊል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ላላወቁ ለማሳወቅ፣ ላወቁትም ለማጽናት መማር አስፈልጓል፡፡ ሮሜ. 8÷30 ‹‹አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፡፡የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፡፡ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው›› እንዲል፡፡
- የከፈሉትን ሰማዕትነት፣ የተቀበሉትን መከራ፣ ያሳዩትን ትእግስትና ጽናት ለምዕመናን ያለውን አርአያነት በቃልና በጽሑፍ ለማስተማር ማንነታቸውን ለማሳወቅ መማር አስፈልጓል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ ላይ፡- ‹‹ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ ደማቸውንም ስለእግዚአብሔር አፈሰሱ ስለመንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሱ›› ብሏል፡፡
- ከእግዚአብሔር ያገኙትን የቃል ኪዳናቸውን በረከት በተለያዩ መንገድ ለእኛ ለምእመናን እንድንጠቀምበት፡፡
- ታሪካቸው የቤተክርስቲያን ታሪክ አካል በመሆኑ የነበሩበት ዘመን፣ ያበረከቱት አስተዋፅኦና አጠቃላይ ሁኔታዎች በወቅቱ የነበረውን የቤተክርስቲያን ሁኔታ ለማወቅ (ለመረዳት) እንማራለን፡፡
- ቅዱሳን የቤተክርስቲያንን ትምህርተ ኃይማኖት፣ ሥርዓትና ትውፊት ለይተው በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት የጻፉትን መጻሕፍት እንድናውቅና ለሕይወት እንድንጠቀምበት ነገረ ቅዱሳንን እንማራለን፡፡
ቅዱሳንን ማወቃችን ምን ጥቅም አለው?
- ሰይጣን የብርሃን መልአክ መስሎ እንዳይገባ መከላከያ ይሆኑናል
- ተኩላዎች በጎችን መስለው እንዳይንቀሳቀሱ እውተኛ እረኛ ይሆኑናል
- ቤተክርስቲያን መታሰቢያቸውን ለይታ ለመፈጸምና ለእኛ ለማሳወቅ ያስችላታል
- ምዕመናን በክርስቶስ የወይን ግንድነት ላይ ቅርንጫፍ በመሆን ብዙ ፍሬ ያፈሩ የኃይማኖት አባቶቻቸውን አውቀው ከአታላዮች፣ ከአስመሳዮች፣ ከሐሳውያን ቅዱሳን እንድንጠበቅ ይረዱናል፡፡
ቤተክርስቲያን ቅዱሳን የምትላቸው እነማንን ነው?
- ቅዱሳን መላእክት፡- ቅዱሳን መላእክት ከማንኛውም ነገር የራቁ፣ ሥርዓታቸውን የጠበቁ፣ እግዚአብሔርን ያወቁ፣ እግዚአብሔርን የሚቀድሱ ስለሆኑ ቅዱሳን ይባላሉ፡፡
ኢሣ. 6÷3 ‹‹አንዱም ለአንዱ፣ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያሉ ይጮሁ ነበር፡፡›› ስለዚህ በባህሪዩ ቅዱስ የሆነውን እግዚአብሔርን ስለሚያመሰግኑ፣ ስለሚቀዱሱ ቅዱሳን ተብለዋል፡፡
- ቅዱሳን አበው፡- መጻሕፍት ሳይጻፍላቸው መምህራን ሳይላኩላቸው በሕገ ልቡና በቃል ብቻ የተላለፈላቸውን ይዘው እንዲሁም በሥነ ፍጥረት በመመራመር ፈጣሪያቸውን አምነው እርሱ የሚወደውን ሥራ የሠሩና በጣኦት አምልኮ ራሳቸውን ያላረከሱ አባቶች ቤተ ክርስቲያናችን ቅዱሳን ትላቸዋለች፡፡ ለምሣሌ አበው ብዙኃን አብርሃም ኩፋሌ 50÷42-44፣ 11÷1
- ቅዱሳን ነቢያት፡- እግዚአብሔር ከማኅፀን ጀምሮ ጠርቶ መርጧቸው ሀብተ ትንቢትን አጐናጽፏቸው ያለፈውንና ወደፊት የሚሆነውን በእርግጠኝነት እየተናገሩ ሕዝቡን ይመክሩትና ይገስጹት የነበሩ ቤተክርስቲያን በቅድስና ማዕረግ የምትጠራቸው አባቶች ናቸው፡፡
2ኛ ጴጥ 1÷25 ‹‹ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ›› እንዲል፡፡
- ቅዱሳን ሐዋርያት፡- በነቢያት የተነገረውን ቃለ ትንቢት መድረሱንና በዘመናቸው መፈጸሙን ለዓለም እንዲያስተምሩ ጌታችን ራሱ ኑ ተከተሉኝ ብሎ የጠራቸውና የመረጣቸው ናቸው፡፡
ዮሐ. 17÷17-19 ‹‹በእውነት ቀድሳቸው ቃልህ እውነት ነው፡፡ ወደዓለም እንደ ላክኸኝ እንዲሁ እኔ ወደዓለም ላክኋቸው፤ እነርሱም ደግሞ በእውነት የተቀደሱ እንደሆኑ እኔ ራሴን ስለእነርሱ እቀድሳለሁ››
- ቅዱሳን ጻድቃን፡- ቅዱሳን ጻድቃን ጌታን አርአያ አድርገው መላ ዘመናቸውን ከጣዕመ ዓለም ተለይተው ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳዋው አስገዝተው በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በምናኔ ጸንተው ድምጸ አራዊትን፣ ጸብአ አጋንንትን፣ ግርማ ሌሊትን ሳይሳቀቁ ዳዋ ጥሰው፣ ደንጊያ ተንተርሰው፣ ጤዛ ልሰው የኖሩ አባቶችን ቤተክርስቲያን በቅድስና ማዕረግ ታከብራቸዋለች፡፡
ማቴ 10÷42 ‹‹ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ያገኛል›› እንዲል፡፡
- ቅዱሳን ሰማዕታት፡- ቅዱሳን ሰማዕታት ጌታችን በጲላጦስ ፊት ‹‹እኔ እውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ›› ዮሐ 18÷37 ያለውን ምስክርነት በመከተል እግዚአብሔርን አንክድም ለጣኦት አንሰግድም በማለት በዓላውያን ነገስታት ፊት ሳይፈሩና ሳያፍሩ ቆመው የመሰከሩትን ቤተክርስቲያን በቅድስና ትጠራቸዋለች፡፡
- ቅዱሳን ነገሥታት፡- እንደ አሕዛብ፣ ዓላማውያን ነገሥታት በሥልጣናቸው በሀብታቸው በሠራዊታቸው ሳይመኩ ኃይማኖት ይዘው ምግባር ሰርተው የተገኙ እንደ ዳዊት ያሉ ቅዱሳን አባቶች ናቸው፡፡
- ቅዱሳን ሊቃውንት፡- ቅዱሳን ሊቃውንት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያልተመሰለውን መስለው የተመሰለውን ተርጉመው በማስተማር መጻሕፍትን በመተርጐም መናፍቃንን ጉባኤ ሰርተው ረትተው ያስተማሩ ቅዱሳን ይባላሉ፡፡
ሮሜ 10÷15 ‹‹መልካሙን የምስራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው››
- ቅዱሳን ጳጳሳት፡- ቅዱሳን ጳጳሳት የካህናትና የምዕመናን፣ የሰማያውያንና የምድራውያን አንድነት የሆነችውን ቤተክርስቲያን በኃይማኖት በመምራት መንጋውን ከተኩላ በመጠበቅ የክርስቶስን ትዕዛዝ የፈጸሙ ቅዱሳን ናቸው፡፡
- ቅዱሳን መነኮሳት (ደናግል)፡- ቅዱሳን መነኮሳት (ደናግል) ከሕገ እንስሳ ሕገ መላእክት ይበልጣል ብለው ራሳቸውን ለክርስቶስ አጭተው ከሴት ወይም ከወንድ ርቀው ስለ መንግሥተ ሰማያት ብለው ራሳቸውን ጃንደረቦች ያደረጉ ናቸው፡፡
- ቅዱሳት አንስት፡- ጌታችን መርጦ ካስከተላቸው 120ው ቤተሰብ 36ቱ ቅዱሳት አንስት ጌታ ሲሰቀል ሳይሸሱ፣ በመቃብሩም በመገኘት፣ የትንሳኤው ምስክርም በመሆን መከራ በበዛበትና በጸናበት የክርስትና ጐዳና የተጓዙ እናቶች፣ እህቶች ሁሉ ቅዱሳት አንስት ይባላሉ፡፡
- ቅዱሳት መካናት፡- ማለት የተለዩ፣ የተከበሩ ሥራዎች ቦታዎች እግዚአብሔር በመዝሙር፣ በቅዳሴ፣ በማኅሌት ይገለገልባቸው ዘንድ መረጣቸው ገዳማትና አድባራት ቅዱሳት መካናት ይባላሉ፡፡
ኢያሱ 5÷15 ‹‹የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ኢያሱን፡- አንተ የቆምክባት ስፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግር አውልቅ አለው››
- ቅዱሳት መጻሕፍት፡- ቅዱሳት መጻሕፍት የሚባሉት የብሉያትና ሐዲሳት፣ የመነኮሳትና ሊቃውንት፣ እንዲሁም አዋልድ መጻሕፍት ናቸው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ስንል የተመረጡ፣ የተከበሩ የተወደዱና የተመሰገኑ መጻሕፍት ማለት ነው፡፡
ቅዱሳን መጻሕፍት ቅዱስ መሰኘታቸው የሰውን ልጅ መነሻና መድረሻ ታሪክ በሦስቱም ሕግጋት የተነሱ ቅዱሳን ጥንተ ክብራቸውን ገድላቸውን ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን ጸጋ እግዚአብሔር ወልድ የሰውን ልጅ ለማዳን ያደረገውን ጉዞ የማዳን ሥራውን ስለያዙ ቅዱሳን ተባሉ፡፡
- ቅዱሳት ሥዕላት፡- በእግዚአብሔር ትእዛዝና ፈቃድ ተስለው የእግዚአብሔር ስም በሚጠራበት ቦታ የሚቀመጡና ከስዕሉ ባለቤት ተራዳኢነትና በረከትን ለማግኘት የሚጠቅሙ የእግዚአብሔር ልዩ ስጦታዎች ናቸው፡፡ ዘፀ. 25÷18-22፣ ዘኁ. 7÷89
ሥጋዊውን ዓለም ከሚያንጸባርቁ ዓለማውያን ሥዕላት ፈጽመው የተለዩ በመሆናቸው ነው፡፡ የቅዲሳኑ ቅድስና ሥዕላቱንም ቅዱሳት አሰኝቷቸዋል ሥዕላቱ በራሳቸው የሚያደርጉት ገቢረ ተአምራት ቅዱሳት አሰኝቷቸዋል፡፡
- ቅዱሳት ንዋያት፡- በእግዚአሔር ቤት ውስጥ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚውሉ ንዋያት ሁሉ የተቀደሱ ናቸው፡፡ ምክንያቱም አገልግሎቱ የሚፈፀመው ቅድስና የባህሪይ ገንዘቡ ለሆነ ለእግዚአብሔር ነውና፡፡
- ቅዱስ መስቀል፡- የጌታችን ቅዱስ መስቀል ሕያው፣ አማናዊ በሆነው በክርስቶስ ደም ከመክበሩ የተነሳ ቅዱስ ተብሏል፡፡
(ቅዱስ ያሬድ ስለመስቀሉ በድጓ ዘክረምት ላይ እንዲህ ብሏል) ‹‹የቅዱሳን ክብራቸው የጻድቃን ሞገሳቸው የዕውራን ብርሃናቸው እነሆ ይህ መስቀል ነው›› ብሏል፡፡
- ታቦት፡- ቤተክርሲያን ቅዱስ ብላ ከምታከብራቸው አንዱ ታቦተ ሕጉን ነው፡፡
ታቦት ማለት በግእዝ ቋንቋ ማዳሪያ፣ ማዳኛ ማለት ሲሆን በዚህ ታቦት ላይ እግዚአብሔር የሚያድርበትና የሚገለጥበት የጽላት ሕጉ ማዳሪያ ነው፡፡ ዘፀ. 25÷22
የቅዱሳን መታሰቢያ በቤተክርስቲያን
- ቤተክርስቲያን የቅዱሳንን ውለታ አትረሳም፡፡ በአጸደ ሥጋ ያሉትን በማገልገል ያረፉትን ቅዱሳንን ደግሞ በማክበር ገድላቸውን በመጻፍ መታሰቢያቸውን ታደርጋለች፡፡
ዕብ. 6÷10 ‹‹እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ አመጸኛ አይደለምና፡፡›› ዕብ. 11÷32……
- ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳንን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በጸበል፣ ቤተክርስቲያን በማነጽ ጽላት በመቅረጽ ታስባቸዋለች፡፡
ኢሣ. 56÷5 ‹‹በቤቴና በቅጽሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋልሁ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ፡፡››
- ቤተ ክርስቲያን በቅዱሳን የልደትና የእረፍት ዕለታት የመታሰቢያ በዓል በማድረግ በቅዳሴና በማኅሌት በማክበር በዓለ ንግሥ ታደርጋለች፡፡ በስማቸው ጠበል ጸዲቅ ታደርጋለች፡፡ ማቴ 10÷40-42
- ሌላው ቤተክርስቲያን ቅዱሳንን የምታስበው የተጋደሉትን ተጋድሎ፣ የደረሰባቸውን ፈተና፣ ያደረጉትን ውጊያ፣ ጦርነት ድልና አክሊል እስካገኙበት ድረስ ያሉትን ገድላቸውን በመጻፍ ታስባቸዋለች፡፡ 2ኛጢሞ 6÷12፣ ይሁዳ ቁጥር 3
ማጠቃለያ እግዚአብሔር ከ22ቱ ስነፍጥረት በቅድስና ማዕረግ ስሙን ቀድሰው ክብሩን እንዲወርሱ አድርገው የፈጠራቸው ቅዱሳን መላእክትንና፣ የሰው ልጅን ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
2006 ዓ.ም © የመ/ገ/ጽ/ቅ/ጊ/ቤ/ክ ሰንበት ትምሕርት ቤት