Description
የቀለበት ቡራኬ
የጋብቻ ሕይወት፣ የሰው ልጅ ፈቃደ ሥጋዉን እንዲፈጽምበት፣ ዘሩን እንዲተካበትና እንዲረዳዳበት እግዚአብሔር አምላካችን ያዘጋጀው ሥርዓት ነው፡፡ በስእለት ወይም በሌላ ምክንያት ለመመንኰስ ከወሰኑ አባቶችና እናቶች በቀር ለሰብአዊ ፍጡር ዂሉ ጋብቻ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ ወይ በጋብቻ አለዚያም በድንግልና መጽናት እንጂ እንዲሁ እየዘሞቱ መኖር ኀጢአት ነው፡፡ ትዳር ለመመሥረት ወስነን ዝግጅት ላይ የምንገኝ ምእመናንም የጋብቻ መሥፈርታችን ሃይማኖትን፣ ክርስቲያናዊ ምግባርንና መልካም ሰብእናን መሠረት ያደረገ ሊኾን ይገባዋል፡፡ ሀብትን፣ ዝናንና ውበትን ምክንያት አድርጎ መተጫጨት መጨረሻው አያምርምና፡፡ እነዚህ ቁሳውያን መሥፈርቶች ከጊዜ በኋላ ሲጠፉ ጋብቻም አብሮ ሊፈርስ ይችላል፡፡ ስለዚህም መሥፈርታችን ከሃይማኖትና ከምግባር ጋር የተገናኘ መኾን ይኖርበታል፡፡ እነዚህ ከተሟሉ ሀብቱና ሌላው ጉዳይ በጊዜ ሒደትና በጥረት የሚመጣ ነውና፡፡
ጋብቻ፣ የመለኮትና የትስብእት ምሳሌ ነው፡፡ ‹‹እፎ ቤተ ነዳይ ኀደረ ከመ ምስኪን፤ እንደ ምስኪን እንዴት ከደሃ ቤት አደረ?›› እንደ ተባለው እግዚአብሔር አምላካችን ለተዋሕዶ የመረጠው የድሆችን ሥጋ ነው፡፡ የተዋሕዶ ምሳሌ የኾነዉን ጋብቻ የምንመሠርት ምእመናንም ሰዎችን ገንዘብ፣ መልክ፣ ዝና የላቸውም ብለን ልንንቃቸውና ከምርጫ ውጪ ልናደርጋቸው አይገባም፡፡ ጋብቻ፣ አንደኛው የሌላኛውን ድክመት እየሸፈነ የሚኖርበት እንጂ በሁለት ፍጹማን ሰዎች የሚመሠረት ሕይወት አይደለም፡፡ ፍጹም አመለካከት ያለዉን ሰው ማግኘት ይከብዳልና፡፡ በመኾኑም ጥንካሬያችንን በመጋራት፣ ድክመታችንን በማስተካከልና በመተራረም ለመኖር መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡
ጠቢቡ ሰሎሞን “እንደ ቀለበት በልብህ አኑረኝ” በማለት እንደ ተናገረው (መኃ. ፰፥፮)፣ ጋብቻ ለሚጠብቁትና ለሚያከብሩት ሰማያዊ ዋጋ የሚያስገኝ የፍቅርና የአንድነት ሕይወት ነው፡፡ ለቃል ኪዳን የሚታሰረው ክብ ቀለበትም የጋብቻ ሕይወት የማይቋረጥ አንድነት መኾኑን የሚያመላክት ምሥጢር አለው፡፡ በመተጫጨትና በቃል ኪዳን ቀለበት የተመሠረተው ጋብቻ በሥርዓተ ተክሊል ይፈጸማል፡፡
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው