Description
መስጠት ማለት በኩራት፣ አስራት፣ መባና ልዩ ስጦታን ለእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት እንዲሆን ማቅረብ ነው። ይኸውም ያለንን ነገር ሁሉ ከእግዚአብሔር እንደተቀበልን ማሳያና ለእግዚአብሔር ያለንን አክብሮት ፍቅርና አምልኮ የመግለጫ መንገድ ነው።
የስጦታ ዓይነቶችና ትርጉማቸው
ሀ. በኩራት – በኩር (የመጀመሪያ) ከሚለው ቃል ነው። በኩራት የእግዚአብሔር ነው – ዘፀ 23፡19፣ ዘሌ 23፡10-11
– በኩራት መስጠት ማለት እግዚአብሔርን በነገሮቻችን ሁሉ ማስቀደም ማለት ነው – ዘኁ 3፡13፣ ዘዳ 15፡19
– የበኩራት ስጦታ ትዕዛዝ ነው – ዘፀ 13፡2፣ ዘዳ 26፡2
– የመጀመሪያውን ስንሰጥ ያለን ነገር ይባረክልናል – 1ሳሙ 2፡20-21
ለ. አስራት – ዘፍ 14፡20፣ ዕብ 7፡4-5
– አስራት በብሉይ ኪዳን ከአስር አንድ እጅ ማለት ነው – ዘፍ 28፡22። አስራት በአዲስ ኪዳን ግን ከአስር አንድ እጅ ባለፈ በዘራኸው ልክ ነው – 2ቆሮ 9፡6-7
– አስራት የእግዚአብሔር ንብረት ነው – ሚል 3፡8-10
– አስራት የሚሰጡ (የሚያስገቡ) ሰዎች በታማኝነት የእግዚአብሔርን ንብረት መልሰው ለእርሱ የሚሰጡ ናቸው – ዘዳ 14፡22-23
– አስራትን በማስገባት (በመስጠት) ውሰጥ በረከት አለ – ሚል 3፡8-10
ሐ. መባ – እግዚአብሔር ለእኛ ከሰጠን ገቢ አስራት አውጥተን ከሚቀረው ድረሻችን ላይ ለወንጌል ስራ፣ ለድሆች መርጃ፣ ለቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የምሰጠው ስጦታ ነው። ይህ አይነቱ ስጦታ በልብ ደስታ በራሳችን ውሳኔ በአቅማጭን መጠንና ከዚያም በላይ የምንሰጠው ይሆናል – ዘፀ 25፡1-5፣ 2ቆሮ 8፡1-2፣ ዘፀ 34፡20
መ. የፍቅር ስጦታ – ለእግዚአብሔር ቤት ስራና ለእግዚአብሔር አገልጋዮች ፍቅርን ለመግለጽ የሚሰጥ ሲሆን በተለያዩ ጊዚያቶች ሊደረግ ይችላል – ሐዋ 11፡27-30፣ ፊሊ 4፡16-18
የምንሰጥበት ምክንያት እና አላማ
ሀ. እግዚአብሔር እንድንሰጥ አዟል – ዘፀ 25፡1-5፣ ዘሌ 25፡31፣ ዘኁ 18፡21
ለ. ስጦታችን የእግዚአብሔርን መንግስት የማስፋፋት ስራና የእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ላይ የሚውል ነው – 1ቆሮ 9፡4-14፣ 2ቆሮ 8፡4፣ ፊሊ 4፡15-18
ሐ. በመስጠት እግዚአብሔርን እናከብራለን፣ እናመልካለን – ምሳ 3፡9-10
መ. በመስጠት የእግዚአብሔርን በረከት እንለማመዳለን – ሚል 3፡10-12፣ ሉቃ 6፡10
ሠ. በመስጠት ለእግዚአብሔር ታማኝ እንሆናል (አንሰርቀውም) – ሚል 3፡8-10
እንዴት መስጠት እንዳለብን?
ሀ. የምንሰጠው አስቀድመን ራሳችንን ለእግዚአብሔር በመስጠት ነው – ሮሜ 12፡1፣ 2ቆሮ 8፡1-5
ለ. የምንሰጠው በሃዘን (በግድ) ሳይሆን በደስታ ነው – 2ቆሮ 9፡7
ሐ. የምንሰጠው እንደገቢያችን ብቻ ሳይሆን ከጉድለታችንም ጭምር መሆን አለበት – 2ቆሮ 8፡1-5
መ. የምንሰጠው ለሰዎች ለመታየት መሆን የለበትም – ማቴ 6፡1
የምንሰጠው በስጦታችን ለመመካት መሆን የለበትም – ሉቃ 18፡9-14
ስለ ስጦታ ያስተማረንና አስቀድመሞ የሳየን ራሱ እግዚአብሔር ነው። ከስጦታዎች በላይ የሆነውን ስጦታ ለሰው ልጆች ሰጥቷል (ዮሐ 3፡16-30፣ ሮሜ 8፡32)። ይህ በምድራዊ ቃላት ሊገለጽ የማይችል ስጦታ ላመኑት ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ አድርጓል። ቤተ ክርስቲያን ይህንን የምስራች ለአለም ሁሉ ለማድረስ እንድንችልና የእግዚአብሔርን ቤት ስራ እንድትሰራ አማኞች የታዘዙትን የፈቀዱትን ስጦታ ለወንጌል መስጠት አለባቸው። ይህም በሕይወታቸው ይበዛላቸዋል።