Lent – ዐቢይ ጾም

Download PDF

“ሑር፥ እምድኅሬየ ፥ሰይጣን፤ ጠላት ሆይ፥ ከኋላዬ ወግድ”

የዐቢይ  ጾም  ጀማሪና  ዓቢይ  ያሰኘው  ምክንያት

ቅዱሳት መጻሕፍት በስፋት እንደሚመሰክሩት ጾም በሕገ ኦሪትም ሆነ በሐዲስ ኪዳን በሚገባ የታወቀና የተረዳ ሥርዓተ ሃይማኖት ከመሆኑም በላይ ከጥንት ጀምሮ ሕዝበ እግዚአብሔር ሲጠቀሙበት የኖረና ያለ ቀዋሚ መንፈሳዊ ሕግ ነው። ለጌትነቱ ክብር ይግባውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንቢቱንና ምሳሌውንም ለመፈጸም ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ በመሔድ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ከጾመና ከጸለየ በኋላ የጽድቅና የመልካም ሥራ ሁሉ ተቃራኒ የሆነውን ክፉውን ጠላት ዲያብሎስን ፍጹም ድል በመንሣት በጥምቀቱ ሀብተ ልደትን ለሰጠን ለእኛም ጾም መንፈሳዊ የድል መሣሪያ እንዲሆን ባርኮልን በቃልና በተግባር በሚገባ አስተምሮናል። አካለ ክርስቶስ የሆነችውና በከበረ ደሙ የተዋጀችው ቤተ ክርስቲያንም አምላኳንና አዳኟን አብነት አድርጋ ዘወትር በጾምና በጸሎት በመትጋት ዘወትር የሚፈታተናትን ጠላት ሰይጣን እንደ ጌታዋ “ሑር እምድኅሬየ ሰይጣን፤ ጠላት ሆይ፥ ከኋላዬ ወግድ” እያለች ፈተናውን በአሸናፊነት በመወጣት ድል ስትነሣበት ኖራለች፤ ዛሬም ወደፊትም ድል ትነሣበታለች።

ሐዋርያዊት የሆነችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በቀኖናዋ የታወቁ ሰባት አጽዋማት አሏት። ከእነዚህም መካከል ተቀዳሚው ዐቢይ ጾም ሲሆን ይህንንም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአድኅኖት ሥራው መጀመሪያ በማድረግ እነሆ ከቆመ ሳይቀመጥ ከዘረጋ ሳያጥፍ፣ አንዳች እህልና ውኃ ሳይቀምስ የጾመው ታላቅ ጾም ነው። በመሆኑም ዐቢይ ጾም ይባላል። ይኸውም ታላቅና ደገኛ ጾም፤ ስለ ሰው ልጅ ፍቅር ሰው የሆነው አምላክ በፈቃዱ የጾመው ጾም ማለት ነው። ደገኛ
ያሰኘውም ሥርዓተ ጾሙ የተመሠረተው ወልደ አብ፥ ወልደ ማርያም በሆነው በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስለሆነና ጥንተ ጠላታችን የሆነውን ዲያብሎስን ጌታችን ፈጽሞ ድል የነሣበት ጾም በመሆኑ ነው። እንደሚታወቀው ዐቢይ ጾም  መክበበ አጽዋማት ነው። ከዚህም ጋር ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን ጾም፣ ጸሎትና ስግደት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳውያን ትጥቆች ናቸው። ስለሆነም እኒህ ትጥቆቻችን የጨለማው ገዥና የሐሰት አባት የተሰኘ ዲያብሎስን እንደ መምህራችን ክርስቶስ ተዋግተን ፍጹም ድል የምንነሣባቸው ልዩ መሣሪያዎቻችን መሆናቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት በግልጥ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ዛሬ ዓለም በልዩ ልዩ ሥልት ብዙዎችን ወደ ራሷ እየሳበች በመሆኗ እነዚህ የከበሩ መንፈሳውያን  ሀብታት ከብዙ ሰዎች ሕይወት በመራቅ ላይ ይገኛሉ። ይህች ዓለም ያስፋፋችው ከንቱ ልማድም ለክርስቶስ ሰማያዊ ርስት ዜጎች የሆኑትን ነፍሳት ብዙም ሳይዋጉ በዚህ ዓለም ገዥ እንዲያው በቀላሉ እንዲማረኩ አድርጓል።

የጾም ጥቅም

ቅዱሳን አበው ሊቃውንት እንዳስተማሩት ጾም የትዕግሥት መማሪያ፣ የአርምሞ መግኛ፣ የአንብዐ ንስሐ ምንጭና የመልካም ተጋድሎ ሁሉ መሠረት ነው። በመሆኑም በመጽሐፈ መነኮሳት የእግዚአብሔር ሰው “ጾም የጸሎት እናት፣ የዝምታ እኅት፣ የእውነተኛ ንስሐ እንባ ምንጭ፣ የተጋድሎ ሁሉ መጀመሪያ ናት” በማለት ታላቅነቷን ይመሰክራል። እኛም መዝገበ በረከት ከሆነው አምላክ ዋጋ እንድናገኝ ጾማችን የልማድ ጾም መሆን የለበትም። ይልቁንም ጾማችን ፍጹም ንፈሳዊነትን የተላበሰና ሥርዓትን የጠበቀ እውነተኛ ጾም መሆን ይገባዋል።

እውነተኛ ጾም

በመሠረቱ ጾም ከእህልና ውኃ ብቻ መከልከል አይደለም። ነገር ግን ጾም ማለት እግዚአብሔር አምላካችንን ከሚያሳዝንብን ተግባር መቆጠብ እንዲሁም ራስንና ሌላውንም ሰው ከሚጎዳ ማናቸውም አድራጎት ሁሉ መከልከል ማለት ነው። ስለሆነም ጾም ሁለንተናዊ የሕይወት ለውጥ ካልታየበት ረብ ጥቅም የለውም። ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅና የቅዱሳት መጻሕፍት ተርጉም የሆነው ቅዱስ ያሬድ “ይጹም ዐይን፥ ይጹም ልሳን፥ ዕዝንኒ ይጹም እሰሚዐ ሕሱም በተፋቅሮ፤ በፍቅር በመጽናት ዓይን ክፉ ነገርን ከማየት ይጹም፣ አንደበትም ክፉ ከመናገር ይጹም፣ ጆሮም ክፉ ከመስማት ይጹም” ሲል በጾመ ድጓው በአጽንዖት የዘመረው ለዚህ ነው። ከዚህም ትክክለኛ ጾም ማለት ሁለንተናዊ ሕዋሳትን ከክፉ አሳብ፣ ንግግርና ተግባር
መከልከል መሆኑን እንገነዘባለን።

ክቡራን  ሆይ

ከመድኃኒታቸን ከኢየሱስ ክርስቶስ አምላካዊ ጉዞ እንደምንረዳው በጾም ጊዜ ሁልጊዜ ፈተና አለ። ምክንያቱም ጾም መንፈሳዊ ሰልፍ ነውና። ይሁን እንጂ በክርስቶስ ያመኑ ሁሉ የጠላትን ፈተናዎች ሁልጊዜ በድል ይወጧቸዋል። እነሆ ፈታኙንም እንደ  መምህራቸው ክርስቶስ “ሑር እምድኅሬየ ሰይጣን፤ ጠላቴ ሰይጣን ከኋላዬ ሒድ” ብለው ድል ይነሱታል። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ሲያስተምር “ወዝንቱ ዘመድ ኢይወጽእ ዘእንበለ በጾም ወበጸሎት” ሲል የጽድቅ ጠላት የሆነው ዲያብሎስ በጾምና በጸሎት ኃይል ካልሆነ በቀር በሌላ ድል እንደማይነሳ በመግለጽ የጾምን ኃይል አስረድቷል። (ማቴዎስ 17፥21) ስለዚህ እኛም በውስጥም በውጭም ያለውን ጠላት ዘወትር ድል ለመንሳት እንድንችል እግዚአብሔር አምላካችን የሚወደውንና የሚፈቅደውን እውነተኛ ጾም ልንጾም ይገባል። (ኢሳይያስ 58)

ክርስቶሳውያን ምእመናንና ምእመናት

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ” (ኤፌሶን 5፥16) ሲል እንዳስገነዘበው ቤተ ክርስቲያን በዘመናችን ከመቼውም በበለጠ አብዝታ ልትጾምና ልትጸልይ ይገባታል። ምክንያቱም አሁን ያለንበት ጊዜ መንፈሳዊነት እየተዘነጋ፣ ዓለማዊነት እየሰለጠነ ሰዎች በሥጋዊ ሐሳብና ስልት ብቻ እየተመሩ ያለበት ፈታኝ ወቅት ነው። ሰይጣን የሕይወት እንጀራ ክርስቶስን በዳቦ፣ የሥልጣናትና የኃይላት ጌታ ወልድን በትዕቢት፣ የዓለማትን ጌታ በኃላፊና ጠፊ ገንዘብ ከፈተነ በእኛ ላይ ልዩ ልዩ ፈተና ቢያመጣ ምን ያስደንቃል? ይህ ረቂቅ ጠላት ብዙዎችን ቢያስትና የፈተናዎቹንም ስልቶች የለዋወጠ ቢታገላቸው ልንደነቅ አይገባም። ምክንያቱም ክርስቶስን በሁለንተናዊ ሕይወታችን ከመሰልነውና በኑሮአችንም ካከበርነው በክፉ ሰይጣናዊ ፈተና ድል አንነሣም። “ከመ እንተ ብእሲ ለጸዊም በውስተ ገዳም ኃደረ። እምኀበ ዲያብሎስ ተመከረ በኃይለ መለኮቱ መኳንንተ ጽልመት ሠዓረ፤ እንደ ሰው ሆኖ ለመጾም ፵ መዓልት ፵ ሌሊት በገዳመ ቆሮንቶስ ኖረ። ከዲያብሎስ ዘንድ በሦስት አርእስተ ኃጣውዕ ተፈተነ፥ ድል ይነሣልን ዘንድ። ፭ ሺህ ከ፭ መቶ ዘመን ሰልጥነው የኖሩትንና የጨለማ ገዥ የሆኑትን ሠራዊተ ዲያብሎስን በጌትነቱ ሻረልን።” እንዲል /አባ ዲዮስቆሮስ/። እንደሚታወቀው በዘመናችን ይህ ጠላት የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን በሐሰት ወሬ፣ በዓለማዊነት፣ በሥጋዊ ጥቅም፣ በሰላምና አንድነት እጦትና በመለያየት ክፉኛ እየተፈታተናት ይገኛል። ይሁን እንጂ እርሱንም ሆነ ማደሪያዎቹን “ስምከ ሕያው ዘኢይመውት፤ ስምህ የማይሞትና የማይለወጥ ዘላለማዊ ነው” ተብሎ የተመሰከረለትንና መግረሬ ፀር የሆነውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሕያውና ቅዱስ ስም ጋሻና መከታ አድርገን “ሑር እምድኅሬየ ሰይጣን” እያልን ልንቃወማቸውና ፊት ልንነሳቸው ይገባል።

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን “ቀድሱ ጾመ፥ ወስብኩ ምሕላ፤ ጾምን ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ።” በሚለው የነቢየ እግዚአብሔር ኢዩኤል ኃይለ ቃል መሠረት በመላው ዓለም የምትገኙ ኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችንን በእግዚአብሔር ቃል
ለማጽናናትና በአንድነት አጽንቶ ለመጠበቅ ታላቅ የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ዘርግታ፣ የሕይወት ማዕድ አዘጋጅታ ለሕዝበ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ሕይወት በእጅጉ የሚጠቅም ሥራ የመስራት መገፈሳዊ ልምድ አላት። ስለዚህ ጌታችን “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” (ማቴዎስ 4፥4) ሲል በአጽንዖት እንደተናገረው ሁላችሁም በትምህርተ ወንጌሉ ፍጹም ተጠቃሚዎች በመሆን በጾምና በጸሎት መትጋትና መበርታት ይገባችኋል። ይህ ከሆነ
ደግሞ የቃሉ ባለቤት እግዚአብሔር ሕይወታችሁን አብዝቶ ይባርካል፣ እርምጃችሁን ያቀናል፣ ዓላማችሁንም ያሳካላችኋል። ክፉ የሚናገሩትን ሳይሆን በጎ የሚያስተምሩትን ስሙ፤ አፍራሾችን ሳይሆን የሚያንጹትን ተከተሉ። እኛ በልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ፈቃድ የምንኖር ስለሆነ ስለራሳችን በአንዳች አንጨነቅ። ይልቁንም የሁላችን እናት የሆነችው የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን፣ የአገራችንና የሕዝባችን ጉዳይ ግን ዕለት ዕለት ሊያሳስበን ይገባል። ምክንያቱም የመንፈሳዊ ሕይዎት ጉድለት በምድራችን ስለበዛ ነው። እነሆ በምድር ያለችው ቤተ ክርስቲያን የሰማያዊት አገራችን የመንግሥተ ሰማያት አካል ናት። በመሠረቱ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የክርስቶስ አካል እንደ መሆኗ በኪሩቤል ላይ በዘላለማዊ ክብሩ ነግሦ ከተቀመጠው ንጉሣችን ጋር አንድ ሆነን ስደቱንና ፈተናውን የምንቋቋምባትና የምንጽናናባት መለኮታዊ ተቋም ናት። ስለዚህ በዓላማዋ እንድትጸና ልንተጋ ይገባል። ስለዚህ በታላቁ ሱባኤያችን ወቅት የዘወትር ምኞታችንና ጸሎታችን የሰላም አምላክ ለአገራችን ፍጹም ሰላምን፣ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሕዝባችን ፍቅርንና አንድነት እንዲሰጥ መሆን አለበት።

ይልቁንም በዚህ ዘመን የቤተ ክርስቲያን አባቶች ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተግተው ሊጸልዩ ይገባል። መዕመናንም ሰለ አባቶች ተግተው ሊጸልዩ ይገባል። እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን የሚል ስሜት በነገሠበትና መደማመጥ በጠፋበት በዚህ ጊዜ
ሁሉንም ወደሚሰማና ለጥያቄዎቻችን ሁሉ ተገቢውን መልስ ወደሚሰጥ አምላክ ከልብ ልንጸልይ ይገባል። ስለ አገራችን ሰላምና ስለ ሕዝባችን ሕይወት ወደ እግዚአብሔር ዘወትር ማመልከት ተገቢ ነው። መድኃኒታችን ክብር ይግባውና በጾሙ ጊዜ ከጠላት ዲያብሎስ ለቀረቡለት ሦስት ፈተናዎች መልስ የሰጠው በቅዱስ ቃሉ መሆኑን ቅዱስ ወንጌል በሚገባ ነግረናል። ይህም በጾማችንና በጸሎታችን ወቅት ለሚያጋጥመን ማንኛውም ፈተና ተገቢውን መልስ የምናገኘው ከእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ያመለክታል። ክርስቶስ ቅዱሳት መጻሕፍትን እየጠቀሰ ለጠላት መመለሱ ለእኛ አርዓያና ምሳሌ ለመሆን ነው። ይኸውም በጾማችን ወቅት ቃለ እግዚአብሔርን አብዝተን ልናነብና በማስተዋል ልንሰማ እንደሚገባን ያስገነዝበናል።

እነሆ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመላው ዓለም ለምትገኙ ኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን ሁሉ ዐቢይ የወንጌል ጉባኤ በወርሀ ጾም የመዘጋጀት ልማድ አላት። ስለዚህ በየአቅራቢያችሁ ባሉት አብያተ ክርስቲያናት ዘወትር በመገኘት ቃለ እግዚአብሔርን ልትማሩ ይገባል። በመላው ዓለም የተበተነው ውድ ሕዝባችንም ቤተ ክርስቲያኑን ነቅቶና ተግቶ ይጠብቅ ዘንድ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን በየጊዜው የሚተላለፈውን መመሪያና መልእክት አክብሮ በመቀበልና ተግባራዊ በማድረግ ለቤተ ክርስቲያን መስፋፋት ሁሉም ተባብሮ እንዲሠራ አደራ እንላለን። እግዚአብሔር አምላክ ቸርነቱ ባርኮ የሰጠንን ይህንን ወርቃማ የሥራ ጊዜ ሁላችንም በሚገባ እንጠቀምበት። ይልቁንም ጊዜው የጾምና የጸሎት ጊዜ ነውና በእውነት ለእውነት እንጹም፣ ለችግሮቻችን ሁሉ ተገቢውን መፍትሔ በወቅቱ ወደሚሰጠን አምላክ በአንድነት እንጸልይ። በመጨረሻም ነቢዩ ኢዩኤል እንደተናገረው ሁላችንም በያለንበት በእውነት ጾምን እንስበክ፥ ምሕላንም እናውጅ።

እግዚአብሔር አምላካችን ጾሙን የበረከት ጾም ያድርግልን።